ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት የባለሃብቶች ሚና ወሳኝ ነው!
አቶ ፈቃዱ ነመራ Fekadu Nemera ነዋሪነታቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ሲሆን ለበርካታ ዓመታት በመንግስት እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር።
በክልሉ ያለውን ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብቶች ለማልማት እና ራሳቸውን ለመለወጥ ባላቸው ትልቅ ፍላጎት የቅጥር ስራቸውን ትተው ወደ ግብርና ኢንቨስትመንት ስራ ለመሰማራት የእርሻ መሬት ወስደው ወደ ስራ ገብተዋል።
በአሶሳ ዞን ሆሞሻ ወረዳ ለግብርና ኢንቨስትመንት የተረከቡትን ቦታ ለግብርና ልማት ምቹ በማድረግ በአካባቢው የሚፈሱ ወንዞችና ምንጮችን በመገደብ 15 ሰው ሰራሽ ሀይቆችን መስራት ችለዋል፤ በዚህም የዓሳ የሚያመርቱ ሲሆን በተጨማሪም ለሚያከናውኑት የግብርና ልማት ስራዎች ትልቅ የመስኖ ውሃ እንዲያገኙ ያስቻላቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የመስኖ አማራጮችን በመዘርጋት በ250 ሄክታር መሬት ላይ 27 አይነት ወቅታዊና ቋሚ ሰብሎችን እያመረቱ ነው።
ዛሬ የአቶ ፊቃዱ ከአትክልት እስከ የቅባት እህሎች፣ ከዓሳ እርባታ እስከ ወተትና ማር ማምረት እንዲሁም የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን በተደራጀና በዘመናዊ መንገድ ያመርታሉ።
አቶ ፊቃዱ በዛሬ ድካም ነገን ማረፍ፤ ለትውልድም መትረፍ በሚል ዕሳቤ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር፣ የገበያን ዋጋ ከማረጋጋት ባሻገር ለኤክስፖርት የሚሆኑ ምርቶችንም ያመርታሉ።
እንደ ሀገር በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር ከ6 ሺህ 200 በላይ ሲሆኑ ከ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ተረክበው እያለሙ ይገኛሉ፡፡





